tg-me.com/kaletsidkzm/9086
Last Update:
#ቅዱስ_ኤፍሬም_ስለ_ልደተ_ክርስቶስ_እንዲህ_አለ፦
ጌታ ሆይ ቅድስት እናትህ ድንግል ሳለች አንተን ፀንሳ በመውለድ እናትነትን ገንዘቧ አደረገች፤ ድንግል ሆና ሳለች ከጡቶቿ ወተት ፈሰሰ፤ ድንግል ከሆነች መሬት ንጹሕ ምንጭ እንዲፈልቅ፤ እንዲሁ ድንግል ከሆነችው እናትህ ጡቶች ወተት ፈለቀ፡፡ እርሱዋ አንተን ብትሸከምህ አንተ ጽንዕ ሰጥተሃት ነው፤ በተራብክ ጊዜ አንተን ከጡቶቹዋ ትመግብህ ዘንድ፣ ነቢዩ ዳንኤል በታላቅ ተራራ የመሰለህ አንተን አንደ ሕፃናት ታቀፈችህ፤ በፈቃድህ የተጠማህ አንተን በእጆቹዋ በፍቅር ትዳብስህ ዘንድ፤ የምህረት እሳት የሆንኽ አንተ ክንዶቿን መለኮታዊው እሳት እንዳይቃጥላቸው ጠበቅኻቸው፡፡
ጌታ ሆይ እናትህ ግሩም የሆኑ ተአምራት የተፈጸሙባት መካን ናት። ወደ እርሱዋ የሁሉ ጌታ የሆነው ገባ፤ የአገልጋዩን አርአያ ነስቶ ተወለደ። የእግዚአብሔር ቃሉ የሆነ እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ ዝምተኛ ሆኖ ተወለደ። ነጎድጓድ የሆነው እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ ጭምት ሆኖ ተወለደ። እረኛ የሆነው እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ በግ ሆኖ በመወለድ በአባግዕ ቋንቋ ተናገረ፡፡
ጌታ ሆይ የእናትህ ማኅፀን ከተፈጥሯዊው ሥርዓት በተቃራኒው ፈጸመ፤ ሁሉን ያከናወነ በባለጸግነቱ ወደ እርሷ ገባ፤ ደሃ ሆኖ ተወለደ። ከሁሉ በክብር የሚልቀው እርሱ ወደ እርሷ ገባ፤ ትሑት ሆኖ ተወለደ። በክብሩ ገናና የሆነው እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ የባሪያውን መልክ ይዞ ተወለደ። ብርቱ የሆነው እርሱ ወደ እርሱዋ ገባ፤ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ሕፃን ሆኖ በማኅፀን ተገኘ። ፍጥረትን ሁሉ የሚመግበው መራብንና መጠማትን ገንዘቡ አደረገ፤ (አጣጣመ) ሁሉን በበረከቱ የሚያለብሰውና የሚያስጌጠው እርሱ ራቁቱን ተወለደ።
እኛን ለማዳን ሲል የእኛን ተፈጥሮ ገንዘቡ ላደረገ ለእርሱ ክብር ምስጋና ይሁን።
መልካም በዓለ ልደት......
BY ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል

Share with your friend now:
tg-me.com/kaletsidkzm/9086